በ2014 በጀት ዓመት የ6 ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ የተቋሙ ሰራተኞችና አመራሮች በተገኙበት ውይይት ተደረገ፡፡

ሲቪል መማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት የስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ በተቋሙ ሰራተኞችና አመራሮች ውይይት ተደርጎበታል፡፡

በእለቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እና ምክትል ዋና ዳይሬከተር አቶ ፋሲካው ሞላ ተገኝተዋል፡፡ ውይይቱን በንግግር ያስጀመሩት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በ2013 በጀት አመት የታዩ ክፍተቶችን በመለየት የማስተካከል ስራ ለመስራት፤ የውስጥ አሰራራችንን የመፈተሽና የማዘመን ስራን ትኩረት በማድረግ፤ አመራሩና ሰራተኛው በአመለካከት፣ በእውቀትና በክህሎት ሊያድግ በሚችልበት የሰው ኃይል ልማት ላይ ትኩረት በማድረግ እንዲሁም የሲቪል ማሀበረሰብ ድርጅቶች እንቅስቃሴ ህግን የተከተለና የሀገራችንን ክብርና ብሄራዊ ጥቅማችንን ያከበረ መሆኑን በጠንካራ የክትትልና ግምገማ ስርዓት ለማረጋገጥ አቅደን ስንቀሳቀስ ቆይተናል ብለዋል፡፡

የተቋሙ ሰራተኞች የኪራይ ሰብሳቢነትንና ብልሹ አሰራርን አምርረው የሚታገሉበት፤ የጋራ እሴቶቻችንን በጋራ የምናሰርጽበትና መልካም አስተዳደርን የምንገነባበትን አሰራር በተጠናከረ መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ በማቀድ የጀመርንት አመት ነበር ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ዓመቱን ስንጀምር እንደስጋት ከለየናቸው ጉዳዮች መካከል ዋነኞቹ ሀገር ሰላምና አለመረጋጋት እንዲሁም የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በእንቅስቃሴያችን ላይ ሊያስከትሉ የሚችሉ ችግሮችን፤ በተለይም በመስክ ክትትል ስራዎችና ለጥናትና ምርምር ስራዎች የሚሆኑ ግብዓቶችን ለመሰብሰብ ልንቸገር እንደምንችል አስበን የነበረ ቢሆንም እንደ አሸባሪው የህውኃት ቡድን ግን ጉዳት ያደረሰብን የለም፡፡ ሌሎች በርካታ እንደስጋት የተያዙ ችግሮች ቢኖሩም የመጀመሪያውን መንፈቅ አመት ከእቅድ አንጻር አጠናቀናል ብለዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ትኩረት ተሰጥቷቸው ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም ግንባታ ስራ ፣የሰው ሃይል ልማት ላይ ትኩረት ማድረግ፣የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሃገርን ጥቅም በመጠበቅ ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል የክትትልና ቁጥጥር ስራ መስራት እንዲሁም መልካም አስተዳደርን የማስፈን ስራዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው የተከናወኑ ተግባራት መሆናቸውን አንስተዋል፡፡ አቅደን ካከናወናቸው አንጻር ያስመዘገብናቸው ስኬቶችም ሆኑ ውስንነቶች ውስጥ የእያንዳዳችን አስተዋጽኦ ያለበት መሆኑን በመረዳት ጠንካራ አፈጻጸሞችን አጠናክሮ መቀጠል እንዲሁም ውስንነቶችንም በማረም በእውቀትና በክህሎት የበቃ፣ ለመማርና ለመለወጥ ዝግጁ የሆነ፣ ቅንና ሁሌም ለውጤት የሚተጋ ከሙስናና ከብልሹ አሰራር የጸዳ የህዝብ አገልጋይ ሰራተኛ ያስፈልጋል ሲሉ ገልጸው እኛ ተግተን ስንሰራ ነው ሌሎች ሊያግዙን የሚችሉት፤ ስለሆነም ከመቼውም ጊዜ በላይ ለሀገራችን ተግተን ልንሰራ የሚገባው ወቅት ላይ እንገኛለን ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

 

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top
Skip to content